በኢዮስያስ ሽመልስ
ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።
1ዩሐ.1፥9
በምድር ላይ ኃያሌ በክርስትና ስም የሚንቀሳቀሱ የእምነት ተቋማት
እንዳሉ ይታወቃል። ነገር ግን የቱንም ያህል በቁጥር ይበርክቱ እንጂ አንድ እውነተኛ መንገድ እንዳለች መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል።
በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ
የሁሉም አባት አለ። (ኤፌ.4፥4)
በመሆኑም እውነቱን ከውሸቱ ለመለየት እንዲቻለን የክርስትና ትምህርት የትኛው ነው? ለሚለው ጥያቄ
ትክክለኛ መልስ ማግኘት ይኖርብናል። ይህን ማድረግ ከተቻለን እውነት ወደምትመስል ሳይሆን ወደ እውነተኛይቱ መንገድ መመለስ
እንችላለን።
ለሰው ቅን የምትመስል
መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።(ምሳ.14፥12) ከዚህ እንደምንረዳው በሰው አስተሳሰብ እውነት የሚመስሉ ሁሉ መጨረሻቸው
ሞት እንደሆነ ነው።
የክርስትና
ትምህርት የትኛው ነው?
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረበት ሰላሳ ሦስት
ዓመት ከስድስት ወር እውነተኛውን የክርስትና ትምህርት ለደቀመዛሙርቱ አስተምሯል። እንዲሁም በምኵራብ እና ህዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች ማስተማሩን መጽሐፍ
ቅዱስ ይነግረናል።
ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ
ምኵራብ ገብቶ አስተማረ።(ማር.1፥21)
በመቀጠልም ለሰው ልጆች ነፍስ ሊከፍል ያለውን ዋጋ ከጨረሰ
በኃላ የመዳንን ወንጌል ለሐዋርያት ሰጥቷል።ከዚህም በኋላ
ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው።(ማር.16፥8)
ወንጌልን እንዲያስተምሩ ስልጣን ከተሰጣቸው ሐዋርያት መካከል የመንግስተ ሰማይ ቁልፍ የተሰጠው ጴጥሮስ መዳን የሚገኝበትን
መንገድ ሲያስተምር፦
ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ
ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።(ሐዋ.ሥራ 2፥38)
ቁ.41 ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ
ተጨመሩ፤
ከላይ መረዳት እንደምንችለው በአንድ ቀን ሦስት ሺህ ነፍስ
ከኃጢያት እና ከሞት እስራት ሊፈቱ የቻሉበት ቁልፍ ንስሐ፥የኢየሱስ
ክርስቶስ ስም ጥምቀት እና የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ነው። ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመዳን አስተምህሮ የማይቀበል ማንኛውም ስመ ክርስቲያን መሳሳቱን
አምኖ መመለስ ይኖርበታል። በተጨማሪ በሐዋ.ሥራ 11፥26 ክርስቲያን የሚለውን ስያሜ ያገኙት በቤተክርስቲያን ሲያስተምሩ የቆዩት
ደቀመዝሙርት ነበሩ።
በቤተ ክርስቲያንም
አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፥ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ።(በሐዋ.ሥራ 11፥26)
ስለዚህ ማንም ሃይማኖተኛ እራሱን እና ተከታዮቹን ክርስቲያኖች
ብሎ ቢጠራም የሐዋርያት ትምህርትን ከጣለ ኢየሱስን የጣለ በመሆኑ ምክኒያት አብ አይኖረውም ክርስቲያንም ሊባል አይችልም።
የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም
የጣለ የላከኝን ይጥላል።(ሉቃ.10፥16)
የእግዚአብሔርን መንግስት ከሚያስወርሰው ትክክለኛ መንገድ ውጪ ሌላ አቋራጭ መንገድ የለም። መሰረቱም አንድ መሰረት የሐዋሪያት እና የነቢያት
መሰረት ነው።
በሐዋርያትና በነቢያት
መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።(ኤፌ.2፥20)
አንዴ ከተመሰረተው መሰረት ውጪ መመስረት ዋጋው በእሳት መቃጠል
መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል።
ከተመሠረተው በቀር
ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።(1ቆሮ.3፥11)
በተለያዩ ዘመናት በሚነሱ ሐሰተኛ ነቢያት የፍልስፍና አስተምህሮ
እንዳንስት ሐዋርያው ጳውሎስ ሲመክረን፦
እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ
መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።(ቆላ.2፥8) ይለናል።
ከሐዋርያት ትምህርት ውጪ ሌላው ልዮ ወንጌል እና የተረገመ በመሆኑ ተከታዮቹን ሊያፀድቅ ከቶ አይቻለውም!!
እርሱ ግን ሌላ ወንጌል
አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ
አንዳንዶች አሉ እንጂ።ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።(ገላ.1፥8)
ማጠቃለያ
ሰዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍቃድ ነው።(1ጢሞ.2፥3-4)
ስለዚህም ሰው ሁሉ ወደ እውነት እንዲመጣ ኢየሱስ ይታገሳል።
ለአንዳንዶች የሚዘገይ
እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ
ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።(2ጴጥ.3፥9)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ
ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ እነርሱ ግን፦ አንሄድባትም አሉ።እኔም የመለከቱን ድምፅ አድምጡ
ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ እነርሱ ግን፦ አናደምጥም አሉ።(ኤር.6፥16)
ዛሬ ይህንን ጽሑፍ የምናነብ ሁሉ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዠ
በመሆን ለነፍሳችን የዘላዓለም እረፍትን ለማግኘት እንድንችል ጌታ ኢየሱስ ይርዳን። አሜን!!!